ልድያ
ልድያ (አሦርኛ፦ ሉዱ፤ ዕብራይስጥ፦ לוד /ሉድ/፣ ግሪክ፦ Λυδία /ሉዲያ/) በምዕራብ ትንሹ እስያ የተገኘ ታሪካዊ አውራጃና መንግሥት ነበር።
በታወቀበት ዘመን ዋና ከተማው ሰርዴስ ሆነ። በአንድ ወቅት የትንሹ እስያ ምዕራብ ክፍል በሙሉ የሉድያ ግዛት ነበረ። በኋለ ዘመን ደግሞ ልድያ የሮማ መንግሥት ጠቅላይ ግዛት ነበረ። መሐለቅ መጀመርያ የተፈጠረው በልድያ ክ.በ. 660 አመት ያሕል እንደ ነበረ ይታመናል።
የታሪካዊው ልድያ ጠረፎች በዘመናት ላይ ይለያዩ ነበር። በመጀመርያ በሚስያ፣ በካርያ፣ በፍርግያና በዮንያ ይወሰን ነበር። በኋላ፣ የንጉሦች አልያቴስና ቅሮይሶስ ሠልፎች ልድያን ሲያስፋፏት፣ ከሉቅያ በቀር ትንሹን እስያ ከሃሊስ ወንዝ ምዕራብ በሙሉ ገዙ። ከፋርስ ወረራ ቀጥሎ ማያንድሮስ ወንዝ በፋርስ መንግሥት የክፍላገሩ ደቡብ ጠረፍ ሆነ። በሮማ መንግሥት ውስጥ ደግሞ የልድያ ጠቅላይ ግዛት በአንድ በኩል ከሚስያና ከካርያ መካከል በሌላውም በኩል ከፍርግያና ከአይጋዮስ ባሕር መካከል ያለው አገር ሁሉ ነበረ።
ቋንቋቸው ሉድኛ በሕንዳዊ-አውሮፓዊ ቋንቋዎች ቤተሠብ ሲሆን በዚሁም ቤተሠብ ውስጥ የአናቶላዊ ቅርንጫፍ አባል ነበር። ስለዚህ የሉዊኛና የኬጥኛ ቅርብ ዘመድ ነው።[1]. ሉድኛም በመጨረሻ እስከ 1ኛ ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ በፊት ድረስ እንደ መነጋገርያ ሆኖ ቆየ።
የልድያ መንግሥት መጀመርያ የተነሣ የኬጥያውያን መንግሥት በ1180 ክ.በ. ገደማ ከወደቀበት ወቅት በኋላ ነበረ።
ቀድሞ በኬጥያውያን መንግሥት ዘመን፣ የአገሩ ስም አርፃዋ ሲሆን ይህ ሉዊኛ የሚናገር አገር ነበር። ይሁንና ክሁሉ ጥንታዊ በሆኑት ኬጥያውያን ሰነዶች የአገሩ ስም «ሉዊያ» ይባላል። በግሪክ ምንጮች ዘንድ ግን፣ የልድያ መንግሥት መጀመርያ ስም ማዮንያ ተባለ፤ ሆሜርም (ዒልያድ ii. 865; v. 43, xi. 431) የልድያን ነዋሪዎች ማዮናውያን (Μαίονες) ይላቸዋል። ሆሜር ደግሞ ዋና ከተማቸውን 'ሰርዴስ' ሳይሆን 'ሁዴ' ይለዋል (ኢልያድ xx. 385)። ሆኖም 'ሁዴ' ምናልባት ሰርዴስ የቆመበት ሠፈር ስም ሊሆን ይቻላል.[2]። ኋላም፣ ሄሮዶቶስ (ታሪኮች i. 7) እንደሚነግረው፣ መዮናውያን ስለ ንጉሳቸው ስለ አቲስ ልጅ ሉዶስ (Λυδός) ስም አዲስ ስያሜያቸውን 'ልድያውያን' (ግሪክ፡ Λυδοί /ሉዶይ/) ተቀበሉ። ይህም የሆነ ከአፈታሪካዊው ሄራክሌስ ሥርወ መንግሥት በፊት እንደ ነበር ይላል። እንደዚህም ሕዝቡ በዕብራይስጥ ሉዲም (לודים) ሲባሉ፣ ምክንያቱም በጥንት ከሉድ ሴም (ዘፍ. 10) እንደ ተወለዱ መሆኑ ይታመናል። በመጽሐፈ ኩፋሌ ምዕ. 9 መሠረት እንደገና የሉድ ርስት ከ'አሦር ተራሮች' ወደ ምዕራብ እስከ 'ታላቁ ባህር' ድረስ ይሠጣል፤ ይህም ማለት የትንሹ እስያ ልሳነ ምድር በሙሉ ነው።
ትልቁ ፕሊኒ (የተፈጥሮ ታሪክ 5:30) እና ሄሮክሌስ እንደ ጻፉት፣ ማዮንያ የተባለ መንደር ለረጅም ዘመን በዙሪያው ይገኝ ነበር።
ሄሮዶቶስ ደግሞ (1.94) የኤትሩስካውያን ሥልጣኔ (በዛሬው ጣልያን) በልድያውያን ሠፈረኞች እንደተመሠረተ በሉዶስም ወንድም በቲሬኖስ እንደ ተመሩ የሞለውን ትውፊት ይጠቅሳል። ነገር ግን የሃሊካርናሦስ ዲዮኒስዮስ ይህን ታሪክ አልተቀበለም፣ የኤትሩስካውያን ባሕልና ቋንቋ ከልዳውያን እጅግ ይለያይ ነበርና።
በፓክቶሎስ ወንዝ የተገኘው የወርቅ ዝቃጅ የልድያ መጨረሻ ንጉስ ቅሮይሶስ ሀብት ምንጭ ሆነ። በአንድ ትውፊት ዘንድ መንስኤው የፍርግያ ንጉስ ሚዳስ 'የወርቅ ዕጆቹን' በውኆቹ ውስጥ ስለ ታጠቡ ነበር።
የፈተና ደንጊያ የተባለው ፈጠራ ዕውቀት በልድያ ከተስፋፋ በኋላ፣ የልድያ ሰዎች ወዲያው ለብረታብረታቸው መደበኛ ጥረት ለማረጋገጥ ቻሉ። ይህ ቀላል መሣርያ ለግሪኮችም «የልድያ ደንጊያ» በመባል ታወቀ። ከዚያ በፊት ከጥንት ጀምሮ ወርቅና ብር በክብደት (ሰቀል) ለሸቀጥ ቢጠቅምም (ለምሳሌ በካሩም)፣ ብዙ ጊዜ ከሌሎች የብረት አይነቶች ጋር ተቀላቅሎ ነበር። አሁን የልድያ ንጉሥ ማሕተም የጥረቱ ማረጋገጫ ሆነ፤ በዚህም አዲስ የመሐለቅ ገበያ መጀመርያ መመሠረት ቻለ።
በሄሮዶቶስ ታሪክ መሠረት፣ ልዳውያን ከሁሉ በፊት የወርቅና የብር መሐለቅ የተጠቀሙት ሰዎች ነበሩ፤ እንዲሁም ቋሚ ሱቆችን መጀመርያ የገነቡት ሕዝብ መሆናቸውን ይመሠክራል[3]።
እነኚህ መጀመርያ መሐለቆች በ660-600 ክ.በ. ገዳማ እንደ ተሰሩ ይታመናል። መጀመርያው መሐለቅ ከኤሌክትሩም (በተፈጥሮ የሚገኝ የወርቅና የብር ቅልቅል) ነው የተሠራ። በእስታቴር ሢሶ ድፍን ሆኖ ክብደቱ 4.76 ግራም ነበር፣ በንጉሡም ምልክት በአንበሣ ራስ ስዕል ይታተም ነበር። አንድ እስታቴር 14.1 ግራም ኤሌክትሩም ነበር። ይህም ለአንድ ወታደር የአንድ ወር ደመወዝ ነበረ።
የልድያ ንጉሥ ቅሮይሶስ ስለ ሀብቱ ስመጥር ሆነዋል። ሆኖም በ558 ክ.በ. ቅሮይሶስ በፋርስ ንጉሥ በ2ኛ ቂሮስ እጅ ድል ስለ ሆኑ መንግሥቱ ወዲያው የፋርስ ክፍላገር ሆነ።
ልድያ በታሪክ 3 ስርወ መንግሥታት ነበሩዋት፦
አትያዶች (1300 ክ.በ) - አፈታሪካዊ ዘመን (ቅድመ ታሪክ)
ሄራክሊዶች (እስከ 695 ክ.በ. ድረስ) - በሄሮዶቶስ ዘንድ ሄራክሊዶች ከጀግናው ሄራክሌስ ትወልደው ለ22 ትውልዶች ከ1197 ክ.በ ጀምሮ ለ505 አመታት ነገሡ። አልያቴስ በ784 ክ.በ. አካባቢ ነገሡ። የዚሁ ሥርወ መንግሥት መጨረሻ ንጉስ ሙርሲሎስ (ካንዳውሌስ) ነበረ። ከ17 አመታት ዘመን በኋላ በባልንጀራው በጉጌስ እጅ ተገደለ።
መርምናዶች
- ጉጌስ ወይም በአሦር ጽሕፈቶች 'የሉዱ ጉጉ' የተባለው በሙርሲሎስ ፈንታ ከ695 እስከ 660 ክ.በ. አካባቢ ነገሡ። በዚህ ዘመን ዘላኖች ኪሜራውያን ሕዝብ ብዙ ከተሞች በልድያ ዘረፏቸው። ጉጌስ ከግብጽ ጋር ስምምነት አድርገው ሠራዊቱን ወደ ግብጽ ልከው ከአሦራውያን ሃያላት ጋር ተጣሉ።
- 2ኛ አርዲስ (660-629 ክ.በ.)
- ሣድያቴስ (629-618 ክ.በ. ገዳማ) - ሄሮዶቱስ እንዳለው ይህ ንጉስ ከሜዶን ነገሥታት ጋር ታግለው ኪሜራውያንንም ከእስያ አባርረው ስምርንስንም ይዘው፣ ሚጢሊኒን ወረሩት።
- 2ኛ አልያቴስ (618-568 ክ.በ.) - የሜዶን ንጉስ ኩዋክሻጥራ ልድያን ባጠቃ ጊዜ፣ ከረጅም ጦርነትና በ593 ክ.በ. በአንድ ታላቅ ውግያ መካከል ግርዶሽ ድንገት መጥቶ ከዚያ ቀጥሎ በኪልቅያና በባቢሎን ነገሥታት አማካይነት ስምምነት ተደረገላቸውና ያንጊዜ ሃሊስ ወንዝ የሜዶንና የልድያ ጠረፍ ሆነ።
- ቅሮይሶስ (568-554 ክ.በ.) - ከዚህ ንጉስ የተነሣ 'እንደ ቅሮይሶስ ሃብታም' ዘይቤ ሆኗል። ቅሮይሶስ በፋርስ ንጉሥ በ2ኛ ቂሮስ ላይ ጦርነት አድርገው በ554 ክ.በ. ተሸንፈው ከዚያ የልድያ መንግሥት ጨረሰና የፋርስ መንግሥት ክፍላገር ሆነ።
- በ554 ክ.በ የፋርስ ንጉስ 2ኛ ቂሮስ ሰርዴስን ይዘውት ልድያ የፋርስ ክፍላገር ሆነ።
- የፋርስ መንግሥት ለመቄዶን ንጉሥ ለታላቁ እስክንድር በወደቀበት ወቅት ልድያ የክፍላገር ስም ሆኖ ቆየ። እስክንድርም ሲሞት መንግሥቱም በአለቆቹ በተከፋፈለው ጊዜ፣ ልድያ ወደ ሴሌውቅያ ተሰጠ። ከዚያ ወደ ጴርጋሞን መንግሥት ተጨመረ። የጴርጋሞን መጨረሻ ንጉሥ አገሩን ለሮማውያን በኑዛዜ ሰጠ።
ሮማውያን ሰርዴስን በገቡበት ጊዜ በ141 ክ.በ. ልድያ ወዲያው በሮማ መንግሥት ውስጥ የእስያ ጠቅላይ ግዛት ክፍል ሆነ። ይህ በጣም ሃብታም ጠቅላይ ግዛት ነበርና አገረ ገዡ ትልቅ ማዕረግ ነበረው።
ዙሪያው ቶሎ የአይሁድ ሠፈረኞችንና የክርስትና ተከታዮችን አገኘ። በሐዋርያት ሥራ 16:14 መሠረት፣ አንዲት ቀይ ሐር ሻጭ ከትያጥሮን 'ልድያ' ተባለች፣ ትያጥሮንም ቀድሞ 'ልድያ' በተባለ አውራጃ ነበረ። በ3ኛ ክፍለ ዘመን ዓ.ም. ክርስትና ከኤፌሶን መቀመጫ በአገሩ ውስጥ ቶሎ ተስፋፋ።
በሮማ ንጉስ ዲዮክሌቲያኖስ ትዕዛዝ 'ልድያ' በ288 ዓ.ም. እንደገና የትንሽ ጠቅላይ ግዛት ስም ሆነ። ዋና ከተማው እንደገና ሰርዴስ ሆነ።
በቢዛንታይን ንጉሥ ሄራክሊዮስ ዘመን (602-633 ዓ.ም.) ልድያ በአናቶሊኮንና ትራቄሲዮን ክፍላገሮች ተከፋፈለ።
ዙሪያው በመጨረሻው በ1382 ዓ.ም. የኦቶማን ቱርክ መንግሥት ክፍል ሆነ። እስከ ዛሬም ድረስ በቱርክ አገር ምዕራብ ይገኛል።
- ^ Lydia at allaboutturkey.com
- ^ ስትራቦ xiii.626 ይዩ
- ^ "Archive copy". Archived from the original on 2001-05-06. በ2001-05-06 የተወሰደ.
- Goldsborough, Reid. የአለሙ መጀመርያ መሐለቅ (እንግሊዝኛ)
- http://www.knaw.nl/publicaties/pdf/20021051.pdf Archived ዲሴምበር 26, 2010 at the Wayback Machine